Academic Regulations

የኮሌጁ ዋና ዋና አካዳሚክ ህጎች

 • የትምህርት ሴሚስተሮች  በዓመት ውስጥ ሶስት ናቸው እነሱም፡-
 • ከመስከረም – ጥር (1ኛ ሴሚስተር)
 • ከየካቲት – ሰኔ  (2ኛ ሴሚስተር)
 • ከሐምሌ- ነሐሴ  (3ኛ ሴሚስተር ወይም የክረምት ሴሚስተር) ናቸው፡፡
 • በሁሉም ሴሚስተሮች መጀመሪያ ላይ ሁልጊዜ ሁሉም ተማሪ የግዴታ መመዝገብ ይኖርበታል:: ማንኛውም ተማሪ ሳይመዘገብ ቢማርና ቢፈተንም ውጤቱ አይያዝም፡፡
 • ለሴሚስተሩ ሬጅስትራር ክፍል ቀርቦ ያልተመዘገበና መታወቂያውን በወቅቱ ያላሳደሰ ተማሪ የኮሌጁ ተማሪ አይደለም፡፡

ሀ/ የተማሪዎች ትምህርት ማቋረጥና የመልሶ ቅበላ ስርዓት

 (Withdrawal & Readmission of Students)

 1. የሰልጣኞች መልሶ-ቅበላ መጠን ለመቀበል በሚኖር ክፍት ቦታ እና በኮርሱ መኖር  የሚወሰን ይሆናል፡፡
 2. መልሶ ቅበላ ማመልከት የሚፈልግ ማንኛውም ተማሪ ቢያንስ የአንድ ሴሚስተር ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቅበታል፡፡ የ1ኛ ዓመት የመጀመሪያ ሴሚስተር ውጤት ያላስመዘገበ ተማሪ መልሶቅበላ ማመልከት አይችልም፡፡
 3. የመልሶ ቅበላ ማመልከቻ ጊዜያት በዓመት ሁለት ብቻ ሲሆኑ እነዚሁም ከኅዳር 1-30 እና ከሚያዚያ 1-30 ብቻ ናቸው፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ለመልሶ ቅበላ ያላመለከተ ሠልጠኝ ሊስተናገድ አይችልም፡፡ የክረምት ሠልጣኞች መልሶ ቅበላ ማመልከት የሚችሉት ከሚያዚያ 1-30 ብቻ ነው፡፡
 4. ሰልጣኞች በሚገጥሟቸው የትምህርት ውጤት ማነስ በራሳቸው ወጭ ለአንድ ጊዜ ብቻ ተመልሰው መግባት ይችላሉ፡፡ ሆኖም የወደቁበትን ሰሚስተር ትምህርት አልፈው በሌላ ሴሚስተር ትምህርት ላይ የመጨረሻ አንድ እድል ይኖራቸዋል፡፡
 5. የሠልጣኞች መልሶ ቅበላ ማመልከቻ በኮሌጁ የአካዳሚክ ካላንደር መሰረት የሚፈፀም ይሆናል፡፡  ሆኖም ግን ማመልከቻው ሰልጣኙ ከለቀቀ ከሦስት ዓመት በኋላ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
 6. የአንደኛ ዓመት አንደኛ ሰሚስተር ትምህርት ውጤታቸው በ1.00 እና 1.49 መካከል የሆነ የመደበኛ፣ የማታና የክረምት 10 + 3 ሰልጣኞች በራሳቸው ወጪ ለመማር የመልሶ ቅበላ ማመልከቻ ማቅረብ ይችላሉ፡፡
 7. የመደበኛ ሠልጣኞች የአንደኛ ዓመት ሁለተኛ ሴሚስተር  አጠቃላይ አማካይ ውጤታቸው በ1.5 እና 1.74 መካከል ከሆነ የመልሶ ቅበላ ማመልከቻ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ የማታ ሠልጣኞች  ደግሞ ሦስተኛውን (የክረምቱን) ሴሚስተር እንዳጠናቀቁ አጠቃላይ አማካይ ውጤታቸው በ1.5 እና 1.74 መካከል ከሆነ ለመማር የመልሶ ቅበላ ማመልከቻ ማቅረብ ይችላሉ፡፡  
 8. የሁለተኛ ዓመትና ከዚያ በላይ ትምህርት ለመቀጠል 1.75 እና በላይ ነጥብ ያላቸው የመደበኛና የማታ ሰልጣኞች ወይም የ3ኛ እና በላይ የክረምት 10+3 ሰልጣኞች በራሳቸው ወጪ ለመማር የመልሶ ቅበላ ማመልከቻ ማቅረብ ይችላሉ፡፡                                                                          
 9. ተቀባይነት ባላቸው ችግሮች ምክንያት ሰልጣኞች በማንኛውም ጊዜ ትምህርታቸው ሊያቋርጡ (withdrawal) ይችላሉ፡፡                                                                                         
 10. ጥሩ የአካዳሚክ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ትምህርታቸውን አቋርጠው ከነበርና እንደገና ለመግባት ከፈለጉ ተቀባይነት ያለው ማስረጃ በማቅረብ የመልሶ ቅበላ ማመልከቻ ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡
 11. በዲሲፕሊን ውሣኔ መሠረት የአካዳሚክ እገዳ የተደረገባቸው ስልጣኞች ትምህርታቸውን ተመልሰው ለመቀጠል ሲፈልጉ ውሳኔዎቻቸው እየታዩ በመልሶ ቅበላ ደንብ መሠረት የሚሰተናገዱ ይሆናል፡፡

ለ/ ከተማሪዎች የሚጠበቅ ውጤት

 • ለመጀመሪያ ዓመት  ሰልጣኞች
 • ማንኛውም ሠልጣኝ በመጀመሪያ ሴሚስተር ውጤቱ ከ1.00 በታች ካስመዘገበ  ከኮሌጁ ጨርሶ ይሰናበታል (Complete Dismissal)፡፡
 • ማንኛውም ሠልጣኝ በመጀመሪያ ሴሚስተር ውጤቱ ከ1.00 እስከ 1.49 ካስመዘገበ ከኮሌጁ ይሰናበታል (Dismissal)፡፡
 • ማንኛውም ሠልጣኝ የመጀመሪያ ሴሚስተር ውጤቱ በ1.50 እና 1.74 መካከል ከሆነ በማስጠንቀቂያ (Warning) ሊቀጥል ይችላል፡፡
 • በመጀመሪያ ዓመት 1ኛው ሴሚስተር ላይ ማስጠንቀቂያ ያልተሰጠው ሰልጣኝና በ2ኛው ሰሚስተር ላይ ከ1.75 – 1.99 ነጥብ ያመጣ በማስጠንቀቂያ ወደ 2ኛ ዓመት ያልፋል፡
 • በመጀመሪያውና በሁለተኛው ሴሚስተር በተከታታይ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው ሰልጣኝ ከኮሌጁ ይሰናበታል (Dismissal)፡፡
 • በመጀመሪያውና በሁለተኛው ሴሚስተር በተከታታይ የተሰናበተ (Dismissal) ሰልጣኝ ከኮሌጁ ጨርሶ ይሰናበታል (Complete Dismissal)፡፡
 • የሁለተኛውን ሴሚስተር ትምህርት በማስጠንቀቂያ የቀጠለ ተማሪ በሁለተኛው ዓመት 1ኛ ሴሚስተር ለመማር አጠቃላይ አማካይ ውጤቱ ከ2.00 ነጥብ በታች ከሆነ ከኮሌጁ ይሰናበታል (Dismissal)፡፡ .
 • የሁለተኛ ዓመትም ሆነ የሦስተኛ ዓመት ሥልጠና የየሴሚስተሩ አማካይ ውጤት 2.00 እና በላይ መሆን አለበት፡፡ በ2ኛና 3ኛ ዓመት ሥልጠና ላይ በ1.75 እና በ1.99 መካከል ውጤት ያስመዘገበ ሠልጣኝ ከኮሌጁ ይሰናበታል (Dismissal)፡፡ ሆኖም ግን  በ2ኛና 3ኛ ዓመት ሥልጠና ላይ አጠቃላይ አማካይ ውጤቱ ከ1.75 በታች ውጤት ያስመዘገበ ሠልጣኝ ከኮሌጁ ጨርሶ ይሰናበታል (Complete Dismissal)፡፡  
 • ለማታ ሰልጣኞች የ2ኛውና የክረምት ሴሚስተር አንድ ላይ ተደምረው እንደ ሁለተኛ ሴሚስተር ይቆጠራሉ፡፡ ለክረምት    ደግሞ የሁለተኛው ክረምት እንደ ሁለተኛ ሴሚስተር ይቆጠራል፡፡
 • የክረምት ተማሪዎች ከ3ኛ ወደ 4ኛ ዓመት ለማለፍ ከ2.00 ነጥብ በታች ከሆነ ወደሚቀጥለው ሴሚስተር አይሸጋገርም፡፡

ሐ/ ተከታታይ ኮርሶችና ኮርስ መድገም

 1. F ይዘው እንዲቀጥሉ የተፈቀደላቸው ሰልጣኞች ለሁለት ጊዜ ብቻ ኮርስ/ኮርሶች መድገም ይፈቀድላቸዋል፡፡
 2.  D ያላቸው ሰልጣኞች ኮርሱን መድገም የሚችሉት ለመመረቂያ የሚጠበቅባቸው ነጥብ የማይሞላ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡  ይህም የሚሆነው መልሶ ቅበላ በገባበት ሴሚስተርና ለምረቃ አለመብቃቱ (Under graduate) ሲረጋገጥ ነው፡፡
 3. በማናቸውም ሥርዓተ ትምህርት መሠረት የኮርሶች ተከታታይነት /Pre-requisite/ የተጠበቀ ይሆናል፡፡ በቀዳሚው ኮርስ “F” ያስመዘገበ ተማሪ ተከታዩን ኮርስ መውሰድ ስለማይችል በቀጣዩ ሴሚስተር መጣል (drop) ይጠበቅበታል ማለት ነው፡፡

መ/ የተማሪዎች ምረቃ (Graduation)

 • የሚመረቅ/የምትመረቅ ተማሪ ሊወስዱ የሚገባቸውን ኮርሶችና ተፈላጊ መጠነ- ግብር (Credit Hours) አሟልቶ/ታ ስለመውሰዱ/ዷ በየትምህርት ክፍሉ እና በሬጅስትራር መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡
  • የማንኛውም ተመራቂ ተማሪ አጠቃላይ አማካይ ውጤት (Cumulative GPA) 2.00 እና በላይ ነጥብ መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪም በዋና የትምህርት መስኮች (major Subjects) አማካይ ውጤት (Cumulative GPA) 2.00 እና በላይ ነጥብ መሆን አለበት፡፡  
  • ማንኛውም ሰልጣኝ “F” ይዞ መመረቅ አይችልም “F” የተገኘበት ኮርስ ደግሞ በመውሰድ ማሻሻል አለበት፡፡
  • ተደግሞ ለተወሰደ ኮርስ የሚመዘገበው ውጤት C ብቻ ነው፡፡